ክንድ የራቀን እንዲያቀርቡበት የቀረበን እንዲያርቁበት ቤዛ ለኲሉ ዓለም ክርስቶስም የራቀ ጽድቃችንን አቅርቦ የቀረበ ኃጢአታችንን አራቀልን። የእግዚአብሔር አሳብ እንደ ምስራቅ የእኛ እንደ ምዕራብ በተራራቀበት ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ብራና በተወጠረው ትከሻው ወደ አባቱ መንግሥት አፈለሰን። በቀደምት አባቶቻችን እንባ ያልተከፈቱ የገነት ደጆች "ጌታ ሆይ፥ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ" በማለት ወለል ብለው ተከፈቱ። ለምን? ስንል ዘመኑ ደርሷልና፣ እርሱም የምሕረት ባለቤት፣ የቸርነት ግምጃ ቤት ነውና ነው።
በቀደመ የገነት ኑሮ አዳም አትብላ/አትለፍ/ የተባለውን ፍሬ/የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ/ በልቶና ተላልፎ ጌታ ቢባል እግዚአብሔርን ቦታ ቢባል ገነትን አጣ። በአዳም ምክንያት የአዳም የዘር ግንድ የሚያገኛቸው ሁሉ የተጎሳቆለና ለኃጢአት ያመቸ ማንነትን ወረሱ። አዳም አንድ ትዕዛዝ "አትብላ"ን ተላለፈ፤ የአዳም ልጅ ቃየን ደግሞ አዳም ካጠፋው የባሰ አጠፋ ወንድሙን ገደለ። እንዲህ እንዲህ እያለ የጽድቅ ሥራ እየተመናመነ፣ አንዱ አንዱን በኃጢአት እየበለጠ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ተፈጸመ። በዚህ ሁሉ ዘመናት ኃጢአት በሰው ላይ እየሰለጠነ ሞትም ገዢ እየሆነ መጣ። በአገራችን ገጠራማ ክፍል ገበሬው በሬውን ጠምዶ ሲያርስ ድንገት በሬው ወደ ግራ ወይ ወደ ቀኝ ዞሮ አቅጣጫ እንዳይቀይርበት የሚወጋበት ጫፏ ላይ መርፌ ያላት መውጊያ ይይዛል፤ ታዲያ በዛች መውጊያ ሸንቆጥ እያደረገ ወደሚፈልገው አቅጣጫ ይወስደዋል።
ልክ እንደዚሁ በዘመናት መካከል ሞት ሰዎችን በመውጊያው እየወጋ ወደሚፈለገው ቦታ ይወስድ ነበር። ይሄ ለምን ሆነ? ስንል ከለበስነው የጎሰቆለ ማንነት የተነሳ የኃጢአት ቅርብ የጽድቅ እሩቅ ሆነን ስለነበር ነው። የኃጢአት ደመወዝ ደግሞ ሞት ነው። አዳም አንዲት ፍሬ በላ፤ እኛ ደግሞ ዛፉን እንዳለ በላነው። በ 5500 የዘመን ሂደት ውስጥ የእግዚአብሔር መንፈስ ለረድኤት ወደ ሕዝቡ ይመጣል እንጂ ከነርሱ ጋር አይኖርም ነበር። በብሉይ የነበሩ አባቶቻችን የእግዚአብሔርን ሕግ መበቅ እየፈለጉ ሥጋቸው ግን ሥጋት ሆኖባቸው መፈጸም አይችሉም ነበር። ስለዚህም መቼ ነው መጥተህ የምታድነን እያሉ ጌታን ለምነዋል። በዚህ ጊዜ ነው የአዳም መድኃኒቱ፣ የሞት ሞቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተገለጠው። በዘመነ ኦሪት ሞት ወደ ሰዎች ሲመጣ የሚያርድና የሚያንቀጠቅጥ ነበር። ሞት ለሞት እንጂ ለሰዎች የደስታ ርዕስ አልነበረም። ለምን ቢሉ የነፍስ ትክክለኛ አድራሻዋ በትክክል ስለማይታወቅ ነው። አሁን በሐዲሰ ኪዳን ግን ሞት የታለህ? እየተባለ በእግር በፈረሰ የሚፈለግ፣ "መውጊያህ ወዴት ነው?" እየተባለ የሚፎከርበትም ሆነ/1ቆሮ 15፥55/።
በዘመነ ሰማዕታት እናቶች ልጆቻቸውን የሚጋብዙት፣ ባልና ሚስት ከነቤተሰቦቻቸው የሚገቡበት፣ ወጣቶች ተጠራርተው የሚጎነጩት ጽዋ ሞት ነበር። አንድ አባት ወደ ሰማዕታት አደባባይ የደም ምስክርነት ለመስጠት ይሄዳሉ፤ ታዲያ መንገድ ላይ ደቀመዝሙሮቻቸው ያገኟቸውና "አባታችን አባኮት ለ'ኛ እንኳን ይኑሩልን አይሂዱ" ቢሏቸው "አባካችሁ ለአምላኬ ለመድኃኒቴ ለኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም የተወደደ መሥዋዕት ልሁንለት ተውኝ" ብለው ወደናፈቁት ሄዱ። እንዴት የሞት ቅጥሩ ተደፈረ... ይሄን የልብ ሙላትስ ምን አመጣው? ስንል ቀድሞ የማንፈጽመው የእግዚአብሔር ሕግ እንዲፈጸም፣ ጸጋ እግዚአብሔርን አጥቶ የነበረ ሰውነታችን በመንፈስ ቅዱስ እንዲደገፍና ሕግን ፈጻሚ እንዲሆን ስለሆነ ነው። በዋናነት ሕግጋተ እግዚአብሔር በሁለት ይጠቀለላሉ ፍቅረ ቢጽ እና ፍቅረ እግዚአብሔር ተብለው። እነዚህም ወደጎን ሰዎችን መውደድ፣ ወደላይ ደግሞ እግዚአብሔርን መውደድና መፍራት ናቸው/ማር 12፥30-31/።
ጌታችን በደብረ ሲና የሰጠውን ሕግ ሳይሽር፣ ሕግ አልጠብቅ ያልን እኛንም ሳያጠፋ ምሕረትና ፍርድን አስተባብሮ አዳነን። ፍርዱን ለራሱ በመስቀል ተቀብሎ ምሕረትና ሕይወትን ለእኛ ሰጠን። ፍርድና ምሕረት የተባበረሉት እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ሰው በፈረደ በዚያው ቅጽበት ምሕረት ማድረግ አይችልም። ምሕረት ሲያደርግም ፍርዱን ትቶ ነው። እግዚአብሔር ግን ለፍርዱ ጥያቄ ለምሕረቱም ገድለት የለበትምና ሁሉን ያስተባብራል። ብዙ የቆሸሸን ብዙ እንዲያጥቡት ብዙ የራቅን እኛን ጌታ በፍቅሩ ብዙ አስጠጋን። ብዙ ተለፍቶበት የመርገም ጨርቅ የተባለ ጽድቃችን፣ ጌታን በማየትና በመስማት ብቻ ብፅእናን አገኘ/ኢሳ 64፥6 - ማቴ 13፥16/።
"በዚህ ዓለም ለሚኖሩት ሰዎች ሁሉ የምታበራ እውነተኛ ብርሃን ስለ ሰው ፍቅር ወደ ዓለም የመጣህ ፍጥረት ሁሉ በመምጣትህ ደስ አለው"/ውዳሴ ማርያም ዘሰኑይ/
መልካም ሰንበተ ክርስቲያን!
ተፈጸመ። ምሥጋና ለእግዚአብሔር ይሁን!

No comments:
Post a Comment