Tuesday, 23 August 2022

አፄ ዘርዓ ያዕቆብ በመልክአ ማርያም ድርሰታቸው

 



አፄ ዘርዓ ያዕቆብ በመልክአ ማርያም ድርሰታቸው እንዲህ ሲሉ ለእመቤታችን ምስጋናን አቀረቡ።  

 

ሰላም ለፍልሰተ ሥጋኪ መካነ ፍሥሓ ምጡቀ፡ በአእባነ ባሕርይ ዘተነድቀ፡ 

ማርያም ድብተራ እንተ ኢትትከደኒ ሠቀ፡ 

ጽሒፈ ውዳሴኪ እምኪ ኀልቀ ሶበ ኮነ ጥቀ፡ ዝናመ ክረምት ቀለመ ወሰማይ ረቀ።


እመቤቴ ማርያም ሆይ ምጡቅና ሩቅ ወደሚሆን የደስታ ቦታ ላረገ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል። ይኸውም ኅብሩ ሊመረምሩት በማይቻል ዕንቁ የታነፀ ሕንፃ ይገኝበታል። ድንግል ሆይ የማቅና የጨርቅ ያይደለ የብርሃን ድንኳን ነሽ። የክረምት ዝናም ቀለም ሰማያት ወረቀት ቢሆኑ ምስጋናህ ተጽፎ የሚያልቅ አይደለም። 


ስብሐት ለኪ ማርያም በኁልቆ ኩሉ ሥዕርትየ

ስብሐት ለኪ ማርያም በኁልቆ ኩሉ አዕፅምትየ 

ስብሐት ለኪ ማርያም በኁልቆ ኩሉ ዘተርእየ

ስብሐት ለኪ ንግሥትየ በኁልቆ ኩሉ ዘኢያስተርእየ 

ስብሐተ ድንግልናኪ ዘልፈ ይነግር አፉየ


እመቤቴ ማርያም ሆይ በራስ ፀጉሬ ቁጥር አመሰግንሻለሁ። በአጥንቶቼ ቁጥር አመሰግንሻለሁ። ድንግል ሆይ በሚታየውና በሚዳሰሰው ሁሉ ቁጥር አመሰግንሻለሁ። 

ንግሥት ሆይ በማይታየውና በማይዳሰሰው ሁሉ ቁጥር ሰላም እያልሁ የድንግልናሽን ምስጋና አፌ ሁል ጊዜ ይናገራል።


ከእመቤታችን ረድኤት በረከት ያካፍለን። 

የአባቶቻችንን መንፈስ ያሳድርብን።

Sunday, 21 August 2022

ወደሰማይ የተወሰደችው ሸማ/ድንግል ማርያም


 ወደሰማይ የተወሰደችው ሸማ/ድንግል ማርያም

 

ቅዱስ ጴጥሮ ከጫማ ሰፊው ስምዖን ቤት በእንግድነት ሳለ ያየው ራእይ ነው፡፡

 "ሰማይም ተከፍቶ በአራት ማዕዘን የተያዘ ታላቅ ሸማ የሚመስል ዕቃ ወደ ምድር ሲወርድ አየ፤

በዚያውም አራት እግር ያላቸው ሁሉ አራዊትም በምድርም የሚንቀሳቀሱት የሰማይ ወፎችም ነበሩበት።

 ጴጥሮስ ሆይ፥ ተነሣና አርደህ ብላ የሚልም ድምፅ ወደ እርሱ መጣ።

 ጴጥሮስ ግን፦ ጌታ ሆይ፥ አይሆንም፤ አንዳች ርኵስ የሚያስጸይፍም ከቶ በልቼ አላውቅምና አለ።

ደግሞም ሁለተኛ፦ እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ።

 ይህም ሦስት ጊዜ ሆነ፥ ወዲያውም ዕቃው ወደ ሰማይ ተወሰደ።" የሐ/ ሥራ 10:11-16፡፡

የራእዩ ትርጉም በጥቂቱ 

ይኽን ራእይ ቅዱስ ኤፍሬም ዘሶርያ እንዲህ ብሎ ተረጎመው፡፡ "አንቲ ውእቱ መንጦላዕት ስፍሕት እንተ ታስተጋብኦሙ ለመሃይምናን ሕዝበ ክርስቲያን፤ ምእመናን ሕዝበ ክርስቲያንን ሰብስባ የያዘች ሰፊ መጋረጃ አንች ነሽ"

ሰፊዋ ሸማ/መጋረጃ እመቤታችን ናት፡፡ 

በአራት ማዕዘን መያዟ፥ 'ርእይ፣ ሰሚዕ፣ አጼንዎ፣ ገሢሥ'በማየት በመስማት በማሽተትና በመዳሰስ ከሚመጣ ኀጢኣት ንጽሕት መኾኗን ያስረዳል፡፡ 

 

በውስጧ ያሉት እንስሳት አራዊትና አዕዋፍ ልዩ ልዩ መልክና ጠባይ ያላቸው የሰውን ዘር ይወክላሉ፡፡

'ተነሥተህ አርደህ ብላ' ያለው፥ አሕዛብ አንገታቸውን  ለስለት እስኪሰጡ የሚያጸናቸውን ትምህርት አስተምራቸው፤ አጥምቃቸው ሲለው ነው፡፡

ይኽን ሦስት ጊዜ ነግሮት ዕቃው/ሸማው #ወደሰማይ #ተወሰደ፡፡

ሸማዋ ድንግል ማርያም ዛሬ በመቃብር የለችም፤ ወደእርሷ የመጣው ልጇ ወደ እርሱ ወስዷታል፡፡

የሚያስደንቀው ነገር የሸማዋ ወደሰማይ መወሰድ አይደለም፤

በሸማዋ ውስጥ ያሉት ነፍሳትም በእርሷ በኩል ወደሰማይ መወሰዳቸው እንጂ፡፡ 'ኦ ምዕራግ እምድር ውስተ ሰማይ፤ ከምድር ወደሰማይ መውጫ ' እንዲላት አባ ሕርያቆስ፡፡

በሸማዋ ወላዲተ አምላክነት የሚያምኑ በቃልኪዳኗ የተማጸኑ ኹሉ አንድ ኾነው ወደ ገነት ወደ መንግሥተ ሰማያት ይገባሉ፡፡

እግዚአብሔር ባከበራትና በመረጣት 'ሸማ'ውስጥ ለሌሉት ሰዎች ያብርህ አዕይንተ ልቦሙ፡፡

ለነሂ ይክፍለነ ነሀሉ ውስተ መንጦላዕት ስፍሕት፡፡

ፍልሰታ



 “ፍልሰታ” የሚለው ቃል ፈለሰ፣ ተሰደደ(ተገለጠ)፣መከፈት፣ መገለጥ፣ የመዝጊያ የመጋረጃ ከሚለው የግእዝ ስርወ ቃል የተገኘ ሲሆን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ትንሣኤ ይመለከታል፡፡ “ፍልሰት” የሚለው ቃል ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር መሔድን ያመለክታል፡፡ “ፍልሰታ ለማርያም” ሲባልም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካረፈች በኋላ ከጌቴሴማኒ ወደ ገነት መወሰዷን (ማረጓን)፣ በኋላም ሥጋዋ በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ለማመልከት የሚነገር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትውፊትና ቀኖና መሠረት ከሰባቱ የአዋጅ አጿማት መካከል አንደኛው ጾመ ፍልሰታ ለማርያም ሲሆን ከህጻናት ጀምሮ እስከ አረጋውያን የሚጾም ታላቅ ጾም ነው፡፡


እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሦስት ዓመት በእናት በአባቷ ቤት፣ ዐሥራ ሁለት ዓመት በቤተ መቅደስ፣ ዘጠኝ ወር በዮሴፍ ቤት፣ ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር፣ ዐሥራ አራት ዓመት በወንጌላዊው በዮሐንስ ቤት ከኖረች በኋላ በ፷፬ ዓመቷ ጥር ፳፩  ቀን ዐርፋለች፡፡ በሐዋርያት ውዳሴ፣ ዝማሬና ማኅሌት ነሐሴ ፲፬ ቀን ከተቀበረች በኋላ እንደሌሎቻችን ትንሣኤ ዘጉባኤን መጠበቅ ሳያስፈልጋት ነሐሴ ፲፮ በልጇ ስልጣን ተነሥታ በይባቤ መላእክት ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በመዝሙሩ “ተለዐለት እምድር ወበህየ ነበረት ዘምስለ ወልዳ በየማነ አብ ወመንፈስ ቅዱስ፤ እመቤታችን ድንግል ማርያም ከምድር ወደ ሰማይ ዐረገች፡፡ በሰማይም ከልጅዋ ጋር በአብና በመንፈስ ቅዱስ ቀኝ ተቀመጠች” በማለት ወደ ሰማይ ማረጓንና በክብር መቀመጧን ተናግሯል፡፡ ከሺሕ ዓመት በፊትም አባቷ ዳዊት “በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” ሲል የተናገረው ትንቢት ይህንኑ የእመቤታችንን ክብር የሚመለከት ነው (መዝ. ፵፬፥፱)፡፡ በዚህች የአስተምህሮ ጦማርም ነገረ ፍልሰቷን እንዳስሳለን፡፡


“እንደ ልጇ ‹ተነሣች፤ ዐረገች› እያሉ እንዳያውኩን በእሳት እናቃጥላት” (አይሁድ)


እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጥር ፳፩ ቀን በ፵፱ ዓ.ም በ፷፬ ዓመቷ ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድና ድካም ባረፈች ጊዜ ቅዱሳን ሐዋርያት ሊቀብሯት ወደ ጌቴሴማኒ ይዘዋት ሔዱ፡፡ በዚህ ጊዜ ጌታችንን የሰቀሉት አይሁድ “እንደ ልጇ ‹ተነሣች፤ ዐረገች› እያሉ እንዳያውኩን በእሳት እናቃጥላት” ብለው ሥጋዋን ሊያጠፉ በዓመፃ ተነሡ፡፡ ከእነርሱም መካከል ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ የአልጋውን አጎበር ይዞ ሊያወርዳት ሲል የእግዚአብሔር መልአክ ሁለት እጆቹን ቀጣው፡፡ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስን ጨምሮ እመቤታችንን በደመና ነጥቆ ወደ ገነት ወስዶ ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጣት፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም እመቤታችን ያለችበት ቦታ እንዲገለጥላቸው ባረፈች በስምንተኛው ወር ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ሱባዔ ገብተው እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ ጀመሩ፡፡



“ተንሥአት እሙታን፡ ማርያም ድንግል ከመ ትንሣኤ ወልዳ ዘልዑል/ እንደ ልጇ ትንሣኤ ባለ ትንሣኤ ተነሳች/” (ቅዱስ ኤፍሬም)


ሐዋርያት እመቤታችን ካረፈችበት ቀን ከጥር ፳፩ ቀን ጀምሮ እስከ ነሐሴ ድረስ ጥያቄያቸውንና ጸሎታቸውን ባያቋርጡም ከሰው ተለይተው ሱባዔ ገብተው ጾም ጸሎት የጀመሩት ግን ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ነው፡፡ ቀድሞስ የክብር ባለቤት የጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ኾነው እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ተሰውራባቸው እንዴት ዝም ብለው ይቀመጣሉ? ቅዱሳን ሐዋርያት ሁለት ሱባዔ (ዐሥራ አራት ቀናት) ካደረሱ በኋላም የነገሩትን የማይረሳ፣ የለመኑትን የማይነሳ እግዚአብሔር አምላካችን ጸሎታቸውን ሰምቶ ነሐሴ ፲፬ ቀን የእመቤታችንን ሥጋ ሰጥቷቸው በክብር ገንዘው በጌቴሴማኒ ቀብረዋታል፡፡ በሦስተኛው ቀንም በልጇ በጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስልጣን፣ እንደ ልጇ ከሙታን ተለይታ ተነሥታለች፡፡መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤያችን በኩር ሆኖ በሞተ በሦስተኛው  ቀን ሙስና መቃብርን (የመቃብርን ሥልጣን) አጥፍቶ ሞትን ድል አድርጎ በገዛ ሥልጣኑ ተነሥቷል፡፡ እናቱ እመቤታችንም በልጇ ሥልጣን፤  እንደ ልጇ ትንሣኤ (ከመ ትንሳኤ ወልዳ ) በሦስተኛው ቀን ተነሥታ ትንሣኤ ዘጉባኤን ሳትጠብቅ በክብር ዐርጋለች፡፡ የቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ የክብርና የሕይወት ትንሣኤ ሲሆን ሁለተኛ ሞትን አያስከትልም ትንሣኤ ዘጉባኤንም አይጠብቅም፡፡


“አይዞህ! አትዘን፤ ባልንጀሮችህ ሐዋርያት ያላዩትን ትንሣኤዬን አንተ አይተሃልና ደስ ይበልህ!” (ድንግል ማርያም)


ይህ ቃል እመቤታችን ለሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ የተናገረችው ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ወንጌለ መንግስትን ሲሰብክ ቆይቶ ደመና ጠቅሶ ከሀገረ ስብከቱ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችን ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ወደ ሰማይ ስታርግ ጠፈር ላይ አገኛት፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ፤ ዛሬ ደግሞ ያንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁን?›› ብሎ ትንሣኤዋን ባለማየቱ ኀዘን ስለ ተሰማው ከደመናው ይወድቅ ዘንድ ወደደ፡፡ “ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ” እንዲል፡፡ እመቤታችንም ‹‹አይዞህ! አትዘን፤ ባልንጀሮችህ ሐዋርያት ያላዩትን ትንሣኤዬን አንተ አይተሃልና ደስ ይበልህ!›› ብላ ከሙታን ተለይታ መነሣቷንና ማረጓን ለሐዋርያት እንዲነግራቸው አዝዛ የያዘቸውን ሰበን ሰጥታ ሰደደችው፡፡ ከዚያም እርሷ ወደ ሰማይ ዐረገች፤ እርሱም ወደ ኢየሩሳሌም ወረደ፡፡ ቅዱስ ቶማስ ትእዛዟን ተቀብሎ በክብር ከተሰናበታት በኋላ ወደ ሐዋርያት ሔዶ እንዳልሰማ እንዳላየ መስሎ ‹‹የእመቤታችን ነገር እንደምን ኾነ?›› ሲል ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም ‹‹አግኝተን ቀበርናት›› ሲሉት “አይደረግም ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር እንደምን ይሆናል?” አላቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ከዚህ በፊት የክርስቶስን ትንሣኤ መጠራጠሩን ጠቅሶ እየገሠፀ መከራከሩንና መጠራጠሩን ትቶ ስለ እመቤታችን መቀበር እነርሱ የሚነግሩትን ዅሉ አምኖ መቀበል እንደሚገባው ለቅዱስ ቶማስ አስረዳው፡፡


“ወንድሞቼ! አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ስታርግ አግኝቻታለሁ” (ቅዱስ ቶማስ)


ቅዱስ ቶማስም የያዘውን ያውቃልና ጸጥ ብሎ የቅዱስ ጴጥሮስን ተግሳጽ ሲሰማ ቆየ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ተቈጥቶ የእመቤታችንን ክቡር ሥጋ ለቅዱስ ቶማስ ለማሳየት ሔዶ መቃብሯን ቢከፍት የእመቤታችንን ሥጋ ሊያገኘው አልቻለም፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ደንግጦ ቆመ፡፡ ቅዱስ ቶማስም ‹‹ወንድሞቼ! አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ስታርግ አግኝቻታለሁ›› ብሎ እመቤታችን የሰጠችውን ሰበን ለሐዋርያት ሰጥቷቸዋል፡፡ ይህ ሰበንም ሊቁ በመልክዓ ማርያም ድርሰቱ “ሰላም ለግንዘተ ሥጋኪ በእደ ሐዋርያት አርጋብ፣ በአፈወ ዕፍረት ቅድው ዘአሣበ ሤጡ ዕፁብ…እመቤቴ ማርያም ሆይ ዋጋው እጅግ ብዙ በሆነና መዓዛው በሚጣፍጥ ሽቱ በሐዋርያት እጅ ለተገነዘው ንጹሕ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል፡፡” እንዳለው ቅዱሳን ሐዋርያት ሞገሳቸውን እመቤታችንን ለመቅበር የገነዙበት ነበር፡፡ እነርሱም በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤና ዕርገት እየተደሰቱ ሰበኑን ለበረከት ተካፍለውታል፡፡ በየሀገረ ስበከታቸውም ሕሙማንን ሲፈውሱበትና ገቢረ ተአምርሲያደርጉበት ኖረዋል፡፡

ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያስተምሩን በቅዳሴ ጊዜ ሠራዒ ዲያቆኑ በሚይዘው መስቀል ላይ የሚታሠረው መቀነት መሰል ልብስ፤ እንደዚሁም አባቶች ካህናት በመስቀላቸው ላይ የሚያደርጉት ቀጭን ልብስና በራሳቸው ላይ የሚጠመጥሙት ነጭ ሻሽ የእመቤታችን ሰበን ምሳሌ ነው፤ቅዱሳን ሐዋርያት ለበረከት ተካፍለውታልና፡፡


“ቶማስ የእመቤታችን ትንሣኤዋንና ዕርገቷን አይቶ እኛ እንዴት ሳናይ እንቀራለን?” (ቅዱሳን ሐዋርያት)


ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ የእመቤታችንን ዕርገት ባየ በዓመቱ ቅዱሳን ሐዋርያት “ቶማስ የእመቤታችን ትንሣኤዋንና ዕርገቷን አይቶ እኛ እንዴት ሳናይ እንቀራለን?” ብለው ከየሀገረ ስብከታቸው ተሰባስበው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋዋን ይሰጣቸው (ዕርገቷን ያሳያቸው) ዘንድ ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ሱባዔ ይዘው ጌታችንን ጠየቁት፡፡ እርሱም ልመናቸውን ተቀብሎ ነሐሴ ፲፮ ቀን እመቤታችንን መንበር፤ ጴጥሮስን ተራዳኢ ካህን፤ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ እመቤታችንንም ሐዋርያትንም አቍርቧቸዋል፡፡ እነርሱም እመቤታችንን በዓይናቸው ከማየት ባሻገር አብረው ሥጋውን ደሙን ተቀብለዋል፡፡


ከነሐሴ ፩ እስከ ፲፭ ቀን ያለው ሁለት ሱባዔ ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ይሁን፡፡ (ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን)


የእመቤታችንን የትንሣኤና የዕርገት ትምህርት መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ከነሐሴ ፩ እስከ ፲፭ ቀን ያለው ሁለት ሱባዔ ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ኾኖ በምእመናን ዘንድ መጾም እንደሚገባው ሥርዓት ሠርተውልናል (ፍት.ነገ.አን.፲፭)፡፡ ይህ ጾምም ‹‹ጾመ ማርያም (የማርያም ጾም)›› ወይም ‹‹ጾመ ፍልሰታ ለማርያም (የማርያም የፍልሰቷ ጾም)›› እየተባለ ይጠራል፡፡ በጾሙም መጨረሻ የቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ ይከበራል፡፡ በእመቤታችን የትንሣኤ በዓል ላይ “ተንሥአት እሙታን ማርያም ድንግል! ከመ ትንሣኤ ወልዳ ዘልዑል” ማለትም “ድንግል ማርያም ከሙታን ተለይታ ተነሣች! ይህውም ልዑል አምላክ ልጇ እንደተነሳው ትንሳኤ ነው!” የሚለውን የምስራች ቃል ምእመናን ይለዋወጣሉ። ይህ የደስታ መንፈስና ስርአት እንደልጇ ዘመነ ትንሳኤ እስከ ነሓሤ 21 ቀን ድረስ ይቀጥላል። የመልክአ ማርያም ደራሲም ‹‹ሰላም ለፍልሰተ ሥጋኪ ደባትረ ብርሃን ኀበ ተተክሉ፤ ለገነተ ጽባሕ በማዕከሉ (እመቤቴ ማርያም ሆይ በምስራቃዊ ተክለ ገነት መካከል የብርሃን ድንኳኖች ወደተተከሉበት ለዐረገ ሥጋሽ ሰላምታ ይገባል)›› ያለውም ይህንን ያመለክታል፡፡


በጾመ ፍልሰታ  የእመቤታችን ከፅንሰቷ ጀምሮ እስከ ዕርገቷ ድረስ ያለው ታሪኳ ይነበባል (ሰዓሊ ለነ ቅድስት/ሰአሊ ለነ ቅድስት)፡፡


በጾመ ፍልሰታ ወቅት በቤተክርስቲያናችን በየቀኑ በማኅሌቱ፣ በሰዓታቱና በቅዳሴው በሚደርሰው ቃለ እግዚአብሔር ነገረ ማርያም ማለትም የእመቤታችን ከመፀነሷ ጀምሮ እስከ ዕርገቷ ድረስ ያለው ታሪኳ፣ ለአምላክ ማደሪያነት መመረጧ፣ ንጽሕናዋ፣ ቅድስናዋ፣ ክብሯ፣ ርኅርራኄዋ፣ ደግነቷ፣ አማላጅነቷ፣ ሰውን ወዳድነቷ በስፋት ይነገራል፡፡ እመቤታችንን ከሚያወድሱ ድርሳናት መካከልም በተለይ ምሥጢረ ሥላሴን፣ ምሥጢረ ሥጋዌንና ነገረ ድኅነትን ከነገረ ማርያም ጋር በማዛመድ የሚያትተው ቅዳሴ ማርያም፤ እንደዚሁም ነገረ ድኅነትን ከምሥጢረ ሥጋዌ (ከነገረ ክርስቶስ) እና ከነገረ ማርያም ጋር በማመሣጠር የሚያትተው ውዳሴ ማርያምም በስፋት ይጸለያል፤ ይቀደሳል፤ ይተረጐማል፡፡ በሰንበታት የሚዘመሩ መዝሙራት፤ በየዕለቱ በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእግዚአብሔር ለተዋሕዶ መመረጧን፣ ዘለዓለማዊ ድንግልናዋን፣ ክብሯን፣ ቅድስናዋን፣ ንጽሕናዋን የሚያወሱ ናቸው፡፡ የእመቤታችን ንጽህና የነገረ ድህነት፣ የጌታችን ቤዛነት መነሻ፣ መሰረት ነውና፡፡


በጾመ ፍልሰታ ገዳማውያን ብቻ ሳይኾኑ ዓለማውያንም ሱባዔ ይገባሉ፡፡


በጾመ ፍልሰታ ገዳማውያን ብቻ ሳይኾኑ ዓለማውያንም በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በእመቤታችን አማላጅነት የሰይጣንን ፈተና ድል ለማድረግ እንዲቻላቸው ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው በየገዳማቱና በየአብያተ ክርስቲያናቱ በዓት አዘጋጅተው፣ ሱባዔ ገብተው፣ ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው አስገዝተው ይጾማሉ፤ ይጸልያሉ፡፡ እንደዚሁም ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ይቀበላሉ፡፡ ይህ ጾም ለእመቤታችን ያለንን ፍቅርም የምንገልጽበት ወቅት ነው፡፡ በተለይ ኦርቶዶክሳውያን ሕፃናት በአብዛኛው ትምህርተ ወንጌል የሚማሩት፤ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን የሚቀበሉት በዚህ በጾመ ፍልሰታ ነው፡፡ ጌታችን በስሙ ሁለትም ሦስትም ኾነን ለጸሎትና ለመልካም ሥራ ብንሰባሰብ እርሱ በመካከላችን እንደሚገኝ የገባልንን ቃል ኪዳን መሠረት በማድረግ (ማቴ. ፲፰፥፳)፣ ሁላችንም በጾመ ፍልሰታ ሳምንታት በጌታችን፣ በእመቤታችንና በቅዱሳን ሐዋርያት ስም በቤተ ክርስቲያን ተሰባስበን ቅዱሳት መጻሕፍትን ከመማር ባሻገር ብንጾም፣ ብንጸልይ፣ ብናስቀድስ፤ እንደዚሁም ሥጋውን ደሙን ብንቀበል በበረከት ላይ በረከትን፤ በጸጋ ላይ ጸጋን እናገኛለን፡፡ በኋላም ሰማያዊውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ እንችላለን፡፡

ከላይ እንደተጠቀሰው በቤተክርስቲያናችን በፆመ ፍልሰታ በተለየ መልኩ ከሚነበቡ፣ ከሚተረጎሙ ቅዱሳት መጻሕፍት አንዱ ውዳሴ ማርያም ነው፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ከደግነቱ የተነሳ እመቤታችን ተገልጣለት ውዳሴ ማርያምን ደርሶ አመስግኗታል፡፡ ምስጋናውም በሰባቱ ዕለታት የተከፈለ ፷፬ ምዕራፎች ያሉት ነው፡፡ ፷፬ መሆኑም እመቤታችን በዚህ ምድር በሥጋ የኖረችበትን ዘመን ያጠይቃል፡፡ ኢትዮጵያዊ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ደግሞ በእያንዳንዱ ምዕራፍ መጨረሻ “ሰዐሊ ለነ ቅድስት/ሰአሊ ለነ ቅድስት” (ቅድስት ሆይ ለምኝልን) የሚለውን ጨምሮበታል፡፡ ሰዐሊ ለነ ቅድስት ተብሎ በዐይኑ ‘ዐ’ ሲጻፍ አዕምሮውን ለብዎውን (ማስተዋሉን) ሳይብን አሳድሪብን ማለት ነው፡፡ ሰአሊ ለነ ቅድስት ተብሎ በአልፋው ‘አ’ ሲጻፍ ለምኝልን ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ከታወቁ የሕግ ምንጮች ከቅዱሳን አባቶቻችን በተማረችው መሰረት “ሰዐሊ ለነ ቅድስት/ሰአሊ ለነ ቅድስት” እያለች እመቤታችን ከተወደደ ልጇ ትለምንልን ዘንድ በጸሎትና በምልጃ ታሳስባለች፡፡


እኛም የእመቤታችንን ዕረፍትና ትንሣኤ በማሰብ ከልጇ ከወዳጇ የሚገኘውን ጸጋና በረከት ተስፋ በማድረግ የአባቶቻችንንና የእናቶቻችንን ፈለግ ተከትለን በየዓመቱ ጾመ ፍልሰታን እንጾማለን፤ የምንችል ደግሞ ንስሐ ገብተን አስቀድሰን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን እንቀበላለን፡፡ ነገር ግን በሕግ የተከለከለ እስኪመስል ድረስ በዚህ ወቅትም ኾነ በሌላ ጊዜ ሥጋውን ደሙን የሚቀበሉ ወጣቶች ጥቂቶች ናቸው፡፡ ስለዚህም አረጋውያንና ሕፃናት ብቻ ሳይኾኑ ወጣቶችም ጭምር የመቍረብና የመዳን ክርስቲያናዊ ተስፋ እንዳለን በመረዳት ራሳችንን ገዝተን፣ ንስሐ ገብተን፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በመቀበል መንግሥቱን ለመውረስ መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡ አምላካችን በማይታበል ቃሉ ‹‹ሥጋዬን የሚበላ፤ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው›› በማለት ተናግሯልና (ዮሐ. ፮፥፶፬)፡፡የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት ጸጋና በረከት አይለየን፡፡ ጽንዕት በድንግልና፣ ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን፣ አዕምሮውን ለብዎውን ሳይብን አሳድሪብን፡፡


ምንጭ፡- ነገረ ማርያም፣ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ፣ ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ፣ መልክአ ማርያም፣ የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገፅ


 



ልዑል ክንዱን ሰደደልን

 


ልዑል ክንዱን ሰደደልን

ክንድ የራቀን እንዲያቀርቡበት የቀረበን እንዲያርቁበት ቤዛ ለኲሉ ዓለም ክርስቶስም የራቀ ጽድቃችንን አቅርቦ የቀረበ ኃጢአታችንን አራቀልን። የእግዚአብሔር አሳብ እንደ ምስራቅ የእኛ እንደ ምዕራብ በተራራቀበት ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ብራና በተወጠረው ትከሻው ወደ አባቱ መንግሥት አፈለሰን። በቀደምት አባቶቻችን እንባ ያልተከፈቱ የገነት ደጆች "ጌታ ሆይ፥ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ" በማለት ወለል ብለው ተከፈቱ። ለምን? ስንል ዘመኑ ደርሷልና፣ እርሱም የምሕረት ባለቤት፣ የቸርነት ግምጃ ቤት ነውና ነው። 


በቀደመ የገነት ኑሮ አዳም አትብላ/አትለፍ/ የተባለውን ፍሬ/የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ/ በልቶና ተላልፎ ጌታ ቢባል  እግዚአብሔርን ቦታ ቢባል ገነትን አጣ። በአዳም ምክንያት የአዳም የዘር ግንድ የሚያገኛቸው ሁሉ የተጎሳቆለና ለኃጢአት ያመቸ ማንነትን ወረሱ። አዳም አንድ ትዕዛዝ "አትብላ"ን ተላለፈ፤ የአዳም ልጅ ቃየን ደግሞ አዳም ካጠፋው የባሰ አጠፋ ወንድሙን ገደለ። እንዲህ እንዲህ እያለ የጽድቅ ሥራ እየተመናመነ፣ አንዱ አንዱን በኃጢአት እየበለጠ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ተፈጸመ። በዚህ ሁሉ ዘመናት ኃጢአት በሰው ላይ እየሰለጠነ ሞትም ገዢ እየሆነ መጣ። በአገራችን ገጠራማ ክፍል ገበሬው በሬውን ጠምዶ ሲያርስ ድንገት በሬው ወደ ግራ ወይ ወደ ቀኝ ዞሮ አቅጣጫ እንዳይቀይርበት የሚወጋበት ጫፏ ላይ መርፌ ያላት መውጊያ ይይዛል፤ ታዲያ በዛች መውጊያ ሸንቆጥ እያደረገ ወደሚፈልገው አቅጣጫ ይወስደዋል። 


ልክ እንደዚሁ በዘመናት መካከል ሞት ሰዎችን በመውጊያው እየወጋ ወደሚፈለገው ቦታ ይወስድ ነበር። ይሄ ለምን ሆነ? ስንል ከለበስነው የጎሰቆለ ማንነት የተነሳ የኃጢአት ቅርብ የጽድቅ እሩቅ ሆነን ስለነበር ነው። የኃጢአት ደመወዝ ደግሞ ሞት ነው። አዳም አንዲት ፍሬ በላ፤  እኛ ደግሞ ዛፉን እንዳለ በላነው። በ 5500 የዘመን ሂደት ውስጥ የእግዚአብሔር መንፈስ ለረድኤት ወደ ሕዝቡ ይመጣል እንጂ  ከነርሱ ጋር አይኖርም ነበር። በብሉይ የነበሩ አባቶቻችን የእግዚአብሔርን ሕግ መበቅ እየፈለጉ ሥጋቸው ግን ሥጋት ሆኖባቸው መፈጸም አይችሉም ነበር። ስለዚህም መቼ ነው መጥተህ የምታድነን እያሉ ጌታን ለምነዋል። በዚህ ጊዜ ነው የአዳም መድኃኒቱ፣ የሞት ሞቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተገለጠው። በዘመነ ኦሪት ሞት ወደ ሰዎች ሲመጣ የሚያርድና የሚያንቀጠቅጥ ነበር። ሞት ለሞት እንጂ ለሰዎች የደስታ ርዕስ አልነበረም። ለምን ቢሉ የነፍስ ትክክለኛ አድራሻዋ በትክክል ስለማይታወቅ ነው። አሁን በሐዲሰ ኪዳን ግን ሞት የታለህ? እየተባለ በእግር በፈረሰ የሚፈለግ፣ "መውጊያህ ወዴት ነው?" እየተባለ የሚፎከርበትም ሆነ/1ቆሮ 15፥55/። 


በዘመነ ሰማዕታት እናቶች ልጆቻቸውን የሚጋብዙት፣ ባልና ሚስት ከነቤተሰቦቻቸው የሚገቡበት፣ ወጣቶች ተጠራርተው የሚጎነጩት ጽዋ ሞት ነበር። አንድ አባት ወደ ሰማዕታት አደባባይ የደም ምስክርነት ለመስጠት ይሄዳሉ፤ ታዲያ መንገድ ላይ ደቀመዝሙሮቻቸው ያገኟቸውና "አባታችን አባኮት ለ'ኛ እንኳን ይኑሩልን አይሂዱ" ቢሏቸው "አባካችሁ ለአምላኬ ለመድኃኒቴ ለኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም የተወደደ መሥዋዕት ልሁንለት ተውኝ" ብለው ወደናፈቁት ሄዱ። እንዴት የሞት ቅጥሩ ተደፈረ... ይሄን የልብ ሙላትስ ምን አመጣው? ስንል ቀድሞ የማንፈጽመው የእግዚአብሔር ሕግ እንዲፈጸም፣ ጸጋ እግዚአብሔርን አጥቶ የነበረ ሰውነታችን በመንፈስ ቅዱስ እንዲደገፍና ሕግን ፈጻሚ እንዲሆን ስለሆነ ነው። በዋናነት ሕግጋተ እግዚአብሔር በሁለት ይጠቀለላሉ ፍቅረ ቢጽ እና ፍቅረ እግዚአብሔር ተብለው። እነዚህም ወደጎን ሰዎችን መውደድ፣ ወደላይ ደግሞ እግዚአብሔርን መውደድና መፍራት ናቸው/ማር 12፥30-31/። 


ጌታችን በደብረ ሲና የሰጠውን ሕግ ሳይሽር፣ ሕግ አልጠብቅ ያልን እኛንም ሳያጠፋ ምሕረትና ፍርድን አስተባብሮ አዳነን። ፍርዱን ለራሱ በመስቀል ተቀብሎ ምሕረትና ሕይወትን ለእኛ ሰጠን። ፍርድና ምሕረት የተባበረሉት እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ሰው በፈረደ በዚያው ቅጽበት ምሕረት ማድረግ አይችልም። ምሕረት ሲያደርግም ፍርዱን ትቶ ነው። እግዚአብሔር ግን ለፍርዱ ጥያቄ ለምሕረቱም ገድለት የለበትምና ሁሉን ያስተባብራል። ብዙ የቆሸሸን ብዙ እንዲያጥቡት ብዙ የራቅን እኛን  ጌታ በፍቅሩ ብዙ አስጠጋን። ብዙ ተለፍቶበት የመርገም ጨርቅ የተባለ ጽድቃችን፣ ጌታን በማየትና በመስማት ብቻ ብፅእናን አገኘ/ኢሳ 64፥6 - ማቴ 13፥16/። 


"በዚህ ዓለም ለሚኖሩት ሰዎች ሁሉ የምታበራ እውነተኛ ብርሃን ስለ ሰው ፍቅር ወደ ዓለም የመጣህ ፍጥረት ሁሉ በመምጣትህ ደስ አለው"/ውዳሴ ማርያም ዘሰኑይ/ 


መልካም ሰንበተ ክርስቲያን!


ተፈጸመ። ምሥጋና ለእግዚአብሔር ይሁን!



Friday, 19 August 2022

"ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳኔን አድርጋለሁ"


 ኪዳን የሚለው ቃል "ቃል" ከሚለው ጋር እየተዛረፈ በብሉይ ኪዳን ለ280 ጊዜ ያህል ሲጠቀስ በአዲሰ ኪዳን ደግሞ ከ32 ጊዜ በላይ ተጠቅሷል፡፡ "ኪዳን" ቃሉ "ተካየደ" ተማማለ፣ ቃል ተገባባ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ "ምሕረት" የሚለው ቃል ደግሞ ማብራሪያ ሳያሻው ምሥጢሩ ከነዘይቤው ከግእዝ የተወረሰ ነው፡፡ ስለዚህ ኪዳነ ምሕረት ማለት የምሕረት፣ የይቅርታ ውል፣ ስምምነት፣ መሐላ ማለት ነው፡፡ ኪዳን ከተራ ውሎችና ስምምነቶች የበለጠ ጽኑና ቀዋሚ ነው፡፡ ከፍ ያለ ክብደትም አለው፡፡


"ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳኔን አድርጋለሁ" ተብሎ በዳዊት መዝሙር እንደተጻፈ እግዚአብሔር ከመረጣቸው ቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ቃል ኪዳን አድርጓል፡፡ ወደፊትም ያደርጋል፡፡ (መዝ88.3) ቃል ኪዳኑም የምሕረት ቃል ኪዳን ነው፡፡


በቅዱሳን አበውና በቅዱሳት እማት እናቶች ታሪክ፣ ገድልና ድርሳን እንደምናነበው እግዚአብሔር ለቅዱሳን ከመሞታቸው አስቀድሞ ይገለጥላቸውና የምሕረት ቃል ኪዳን ይሰጣቸው ነበር፡፡ የእግዚአብሔር የምሕረት ቃል ኪዳን በቅዱሳኑ ሕይወት ዙሪያ ብቻ የሚያተኩር አይደለም፡፡ ለስማቸው፣ ለመስቀላቸው፣ ለልብሳቸው ገድላቸውን ከትቦ ለያዘ መጽሐፍ፣ አልፎ ተርፎም ለረገጡትና አፈርና ለተጋደሉበት ቦታ ሁሉ ተርፎላቸዋል፡፡ ስለዚህ ልዩ ልዩ ቃል ኪዳን የተገባላቸው ቅዱሳት መካናት ሞልተዉናል፡፡


ለቅዱሳን ከሞት አስቀድሞ የእግዚአብሔር መገለጥ ወይም የሚሞቱበትን ጊዜና የአሟሟታቸውን መንገድ ገልጦ መንገር በቅዱሳት መጻሕፍት የተለመደ ነው እንጂ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ጌታ ለቅዱስ ጴጥሮስ እንዴት ባለ አሟሟት እንደሚሞት ነግሮታል፡፡ (ዮሐ21.19 2ጴጥ1.14) ቅዱስ ጳውሎም ስለሚሞትበት ጊዜ ተነግሮታል፡፡ (የሐዋ20.25 የሐዋ21.10-13) "ከሞቱ አስቀድሜ እገለጥለታለሁ" እንዲል፡፡ (ሰኔ ጎልጎታ)


እግዚአብሔር ከሞታቸው አስቀድሞ በመገለጥ ለቅዱሳን የምሕረት ቃል ኪዳን የሚሰጣቸው በእነርሱ በጎ ሥራ ከእነርሱ በኋላ ያሉ የሰው ልጆችን ለመጥቀም ፈልጎ ነው፡፡ ተጠቃሚዎቹ ራሳቸው ናቸው እንዳይባል ወደ ሞት አፋፍ የተጠጉ ከመሆናቸውም ባሻገር ለቃል ኪዳን የበቁት የሚጠቀሙበት በጎ ሥራ በመሥራታቸው ነው፡፡ የሰው ልጆች ያለፉ ቅዱሳንን በመዘከር የቃል ኪዳናቸው ተጠቃሚ ሲሆኑ ቅዱሳኑ ግን ከመታሰብ በቀር በሰው በኩል የሚያገኙት ምንም ጥቅም የለም፡፡ ቅዱሳን የምሕረት ቃል ኪዳን ሲቀበሉ ለወገናቸው መትረፋቸውን ያመለክታሉ፡፡


የምሕረት ቃል ኪዳን ለምን ያስፈልጋል ቢባል ሕግ መተላለፍ ካለ ሁልጊዜ ተጠያቂነት ወይም ቅጣት ይኖራል፡፡ ይህም በአዳም ይታወቃል፡፡ የሰው ልጆች ደግሞ ከተጠያቂነት ነጻ የሚያደርግ ፍጽምና ይዘው አይገኙም፡፡ በዚህ ምክንያት ቅጣት እንዳያገኛቸው የሚድኑበትን በርካታ መንገዶች እግዚአብሔር አዘጋጀ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የምሕረት ቃል ኪዳን ነው፡፡


የምሕረት ቃል ኪዳን ሁሉ በጎ እንድንሠራ የሚያበረታታ ነው፡፡ ይህም ዘወትር ከቃል ኪዳኑ ጋር ተያይዘው በሚቀመጡ ግዴታዎች ይታወቃል፡፡ ለበጎ ሥራ ምክንያት የማይሆን ባዶ የምሕረት ቃል ኪዳን የለም፡፡ ‹‹ስምሽን (ስምህን) የጠራውን፣ ዝክር ያዘከረውን፣ የተራበ ያበላውን፣ የተጠማ ያጠጣውን፣ የታረዘ ያለበሰውን፣ እንግዳ በስምህ (በስምሽ) የተቀበለውን፣ ገድልህን ያነበበውን፣ የሰማውን፣ የተረጎመውን ወዘተ ኃጢአቱን ይቅር እለዋለሁ፣ እምረዋለሁ›› የሚሉ ቃል ኪዳናት በሙሉ ከባዱ መልካም ሥራ ባይቻለን እንኳን ቀላሉን መሥራት እንዳለብን ግዴታ የሚጥሉ ናቸው እንጂ አንዳንዶቸ እንደሚያስቡት መልካም እንዳንሠራ የሚያሳንፉ አይደሉም፡፡ ከዚህ ይልቅ ለበጎ ሥራ የሚያነሣሡና የታዘዙትን መሥራት ያልተቻላቸውን ሰዎች ተስፋ ሳይቆርጡ እስከመጨረሻው ሰዓት የሚድኑበት መንገድ እንዳለ አውቀው የተቻላቸውን እንዲያድርጉ የሚጠቁሙ ናቸው፡፡


የእግዚአብሔር ቸርነት ከአእምሮ በላይ ነው፡፡ ይህም ሰዎች በእግዚብሔር ቸርነት ላይ በሚያነሡት ጥያቄ ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ፡ እግዚአብሔር በዜና ገድላቸው እንደምናነበው ለብዙ ቅዱሳን "እስክ አሥር፣ ሠላሳ፣ ሃምሳ አምስት ወዘተ ትውልድ ድረሰ እምርልሃለሁ" እያለ የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል፡፡ ይህን በማንበብ እምነት የጎደላቸው አንዳንዶች "ይህ እንዴት ይሆናል?" እያሉ ይጠይቃሉ፡፡ ይህ ብቻ በራሱ የፈጣሪ ቸርነት ከሕሊና በላይ መሆኑን አያስረዳም?


ፈጣሪ ስለ ፈራጅነቱና ስለ መሐሪነቱ ሲናገር ‹‹በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኃጢአት በልጆች ላይ የማመጣ ለሚወዱኝ ትእዛዜን ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝ፡፡›› ይላል፡፡ (ዘጸ20.2-6) ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እስከ ሺህ ትውልድ የሚደርስ የእግዚአብሔርን ምሕረት በመናገሩ በአዋልድ መጻሕፍት ላይ ያለው የሠላሳና የሃምሳ ትውልድን ምሕረት የሚያወሳው ኃይለ ቃል ሊስተባበል አይቻልም፡፡ ያን ማክፋፋት ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እንደመቃወም ይቆጠራልና፡፡


ዓለም ከተፈጠረች ሰባት ሺህ አምስት መቶ ዓመት ገደማ ሊሆናት ነው፡፡ የሰው ልጅን አማካይ እድሜ እጅግ አሳንሰን በመቁጠር የአንድ ትውልድ ዘመን ሠላሳ ዓመት ነው ብንል እንኳን ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ያለው ትውልድ ከሁለት መቶ ሃምሳ አይበልጥም፡፡ በዚህ ዓይነት ደግሞ እስከ ዓለም ፍጻሜም ብንቆጥርና ብናሰላም የትውልድ ቁጥር እንኳን አንድ ሺህ ሊደርስ ወደ አምስት መቶም አይጠጋም፡፡ ነገር ግን ፈጣሪ የሚወደውና ትእዛዙን የሚጠብቅ እውነተኛ ሰው ከተገኘ ያን ያህል ትውልድ አይኖርም እንጂ "እስከ ሺህ ትውልድ" ድረስ እንኳን ይቅር ሊል ቃል ኪዳን ገብቷል፡፡ ይህ የሚያሳየው የእግዚአብሔርን የቸርነት ስፋት ነው፡፡ ሺህ ትውልድ ስለሌለ እግዚአብሔር ሺህ ትውልድ ሊምር አይችልም አይባልም፡፡ ከዚህ አንጻር የፈጣሪን ቃል ኪዳን ከመሐሪነቱ አንጻር እንጂ ከተፈጻሚነቱ አንጻር ሊመለከቱት አይገባም፡፡


ፈጣሪ ለቅዱሳኑ በየዕለቱ ብዙ ነፍሳትን ከሲዖል እንዲያወጡ የምሕረት ቃል ኪዳን ሊሰጣቸው ይችላል፡፡ የተሰጣቸውም ቅዱሳን አሉ፡፡ ነገር ግን ተፈጻሚነቱን ስንመለከት በቀን የተባለውን ያህል ነፍሳት ከሲዖል ሊወጡ ወይም አንድም ነፍስ ከሲዖል ላትወጣ ትችላለች፡፡ ይህ ግን በተገባላቸው ቃል ኪዳን ላይ ምንም ዓይነት አሉታ የለውም፡፡ ምክንያቱም ለቅዱሳኑ ይህ ቃል ኪዳን ሲሰጥ ሲዖል ካለችው ነፍስ ደግሞ የሚጠበቅ ነገር ይኖራልና፡፡ ያን የምታሟላ ነፍስ ካልተገኘች ቃል ኪዳኑ ተፈጻሚ አይሆንም፡፡ ይህም በመሆኑ ቃል ኪዳኑ ከንቱ ነው አይባልም፡፡ ከላይ እንዳየነው ተፈጻሚ ሊሆን ባለመቻሉ ብቻ ለሺህ ትውልድ የተገባው ቃል ኪዳን ከንቱ ነው ሊባል አይቻልምና፡፡


"ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳኔን አደርጋለሁ" ባለው መሠረት ጌታ ከእመቤታችን ጋር ብዙ ቃል ኪዳን አድርጓል፡፡ እርሷ የተመረጠች ብቻ ሳትሆን ከተመረጡትም ሁሉ የተመረጠች ናትና፡፡ ከቅዱሳን ሁሉ እመቤታችን ድንግል ማርያም በሁሉም ረገድ እንደምትበልጥ ከተሰጣቸውም የምሕረት ቃል ኪዳን ለሷ የተሰጣት ኪዳን በእጅጉ ይበልጣል፡፡ በዚህም ምክንያት ድንግል ማርያም በተሰጣት ቃል ኪዳን ተለይታ ትታወቃለች፡፡ ማለትም ትጠራበታለች ኪዳነ ምሕረት ትባላለች፡፡ ስለዚህ የኃጥአን ሁሉ ዓይን የእርሷን የምሕረት ቃል ኪዳን ተስፋ ያደርጋል፡፡


ድንግል ማርያም በቃል ኪዳኗ አትለየን!


 


ውሉደ ኤስድሮስ ሰንበት ትምህርት ቤት መንፈሳዊ blog

 


ይህ የመካነ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተክርስቲያን ውሉደ ኤስድሮስ ሰንበት ትምህርት ቤት መንፈሳዊ blog ነው፡፡ የውሉደ ኤስድሮስ ሰንበት ት/ቤት መንፈሳዊ ጽሑፎች ፣ ወቅታዊ ሁኔታዎች ፥ መረጃዎችን እንዲሁም ማስታወቂያዎች በዚኽ ገጽ ለተከታታዮቹ ይተላለፋሉ።


sonsofesdrosundayschool.blogspot.com


አፄ ዘርዓ ያዕቆብ በመልክአ ማርያም ድርሰታቸው

  አፄ ዘርዓ ያዕቆብ በመልክአ ማርያም ድርሰታቸው እንዲህ ሲሉ ለእመቤታችን ምስጋናን አቀረቡ።     ሰላም ለፍልሰተ ሥጋኪ መካነ ፍሥሓ ምጡቀ፡ በአእባነ ባሕርይ ዘተነድቀ፡  ማርያም ድብተራ እንተ ኢትትከደኒ ሠቀ፡  ጽሒፈ ...